የተወደዳችሁ አድማጮቼ ከዚህ ቀጥሎ የምታደምጡት መዝሙር በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ ፲፭ ከቁጥር ፲፩ ፬ ድረስ በተፃፈው የኮብላይ ልጅ ታሪክ የተወሰደ መሆኑን እያስታወስኩ በዚህ ታሪክ ምሳሌነት የእግዚአብሔር ንአባታዊ እና ዘለዓለማዊ ፍቅር አሳስባችኋለሁ ። በምታደምጧቸው ዝማሬዎች ሁሉ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ። አሜን ። አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x) መስሎኝ ነበር እኔ እራሴን የገዛሁ ንብረቴን ሰብስቤ ሩቅ ሃገር ተነሳሁ ለካስ ልጅ ኖሬያለሁ ምራቄን ያልዋጥኩኝ ለወፍ ለአሞራ ያለኝን በተንኩኝ ጉልበቴም ደከመ ሕይወቴም ባከነ ለካስ አባት ኖሮዋል ጉዴን የሸፈነ አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x) ወዳጄ ነበረ ካለኝ ያካፈልኩት ያጣሁ የነጣሁ እለት ከቦታው አጣሁት ሁሉም በር ዘግቶ አላውቅህም አለኝ የሚያዝንልኝ አጣሁ ሰው ሁሉ አገለለኝ አየሁ ተገነዘብኩ ወዳጅ ማንነቱን ማን ይሆንለታል ለሰው እንደ አባቱ? አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x) ሰርቼ እንዳልበላ ጨርሶ የለኝ ሞያ ተደብቄ ኖርኩኝ በአባቴ ጉያ ጉዴ ተገለጠ ታየ ገበናዬ ከእሪያዎች ጋር ሆነ መዋያዬ ዘበኝነት አጣሁ ጠፋኝ መላ ቅጡ ለካስ ማእረግ የለም ከአባት ቤት ከወጡ አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x) እኔን ያየኝ ይቀጣ ይማር ከሕይወቴ እርቃናዬን ቀረሁ በአባካኝነቴ ሳለሁ ባባቴ ቤት ወዜን ያየ ማነው? ያስብ ጠንቀቅ ይበል ይህ ዓለም ክፉ ነው አጫርሶ ዝም ይላል ምንም ይሁን ምንም የአባት ቤት ይሻላል አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x) አዋጅን የምትሰማ ያለህ የትም ቦታ ጨለማ የዋጠህ የጠፋህ ከጌታ እንጀራውን በልተህ ፈውሱን ተቀብለህ ድርሻህን በመውሰድ የሄድከው ኮብልለህ እስኪ መለስ በል ወደ ጥንቱ ቤትህ አይጨክንብህም ርህሩህ ነው አባትህ ለጣትህ ቀለበት ለእግርህ ጫማ ያጐናፅፍሃል በመንፈሱ ሸማ ፍሪዳ ይታረድ ወገን ደስ ይበለው ለነገ አታሳድር መዳንህ ዛሬ ነው አዝ፦ ወደ አባቴ ወደ ቀድሞ ቤቴ እመለሳለሁ እንደ ልጁም ባይሆን እንደ ባሪያው እኖራለሁ (2x)